ከታሪክ ማህደር ክፍል 1

 ከታሪክ አለመማር ለውድቀት ይዳርጋል

★★★★★★★★★★★★★★★★

‹‹ይገሰፁ ዘንድ ቃላችን እንዲደርሳቸው አድርገናል።›› (ቁርኣን 28÷ 51)

                         ★★★


 ታሪክ ዛሬ ላይ ሆነን የሰው ልጆችን የትላንት ሕይወትን እንድንመለከተው ይረዳናል፡፡ በመሆኑም ታሪክ እጅግ ጠቃሚ የዕውቀት ዘርፍ ነው፡፡ የሰው ልጆት ያለፉበትን ጐዳና፤ ታሪካዊ ክስተቶችን፤ የጥፋትና የልማት አብነቶችን ያሳውቀናል፡፡ ከእነሱ ታሪክም ለዛሬ ስንቅ የሚሆነንን በርካታ ቁም ነገሮችን እንቀስምበታለን፡፡ ከውድቀታቸው የውድቀትን ምክንያቶች እናውቅበታለን፡፡ ከስኬታቸውም የስኬትን ምስጢር እንማርበታለን፡፡ ከትግላቸው አዋጭ የሆነውን የትግል ስልት  እንለይበታለን፡፡ ጽናታቸው ደግሞ የጽናት አብነት ይሆነናል፡፡ ለአብነት ያክልም የዚህ መጽሐፍ ትኩረት የሆነውን የሙሳንና የፊርዐውንን ታሪክ እንመልከት፡፡ ከሁለቱ የትግል ታሪክ እስካሁን በርካታ ቁም ነገሮችን ጨብጠናል፡፡ ለአብነትም የሙሴ ጽናትን ተረድተናል፡፡ ታሪኩን በጥሞና ስናነበው ለኛም ጽናትን ይለግሰናል፡፡ ቁርኣንም ይህንኑ የሙሳን ታሪክ ጨምሮ የመልዕክተኞችን ሁሉ ታሪክ መተረኩ ጽናት እናገኝበት ዘንድ መሆኑን እንዲህ ይገልጸዋል፦ 


      “ይህን ሁሉ (የቀደምት) መልዕክተኞች ታሪክ÷ በርሱ ልብህን ልናፀና ተረክንልህ፡፡…” (ሁድ÷ 120)

ታሪክን ስንረዳ የማስተዋል አቅማችን ይጨምራል፡፡ ነገሮችን የማስተንተን ችሎታችን ይጐለብታል፡፡ የምናደምጠውን ነገር የምንረዳበት ዕድላችን ይልቃል፡፡ በመሆኑም የቀደምት ሕዝቦችን ታሪክ÷ የነገሥታቱን አሻራ እና ቅርሶችን ስንመለከት ዘርፈ ብዙ ዕውቀቶችን እንቀስማለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በምድር ላይ በመጓዝ ታሪክን እንድናጠና የሚጋብዘን ለዚህም ነው፡፡ እንዲህ ብሏል፦ 


     “የሚያስተውሉበት ልቦና፤ የሚሰሙበት ጆሮ ይኖራቸው ዘንድ በምድር ላይ አይጓዙምን? እነሆ ዓይኖች አይታወሩም፡፡ የሚታወሩት በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ናቸው፡፡” (አል-ሐጅ÷ 46)


ታሪክን በአስተውሎ በማስተንተን ስናጠናው በውስጡ በእያንዳንዱ ዘርፍ ተሞክሮዎችን እንቀስምበታለን፡፡ ተግሳጽና ትምህርትም እናገኝበታለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን ታሪክን ከተረከ በኋላ እንዲህ ይላል፦ 


 “ታሪካቸው በርግጥ ለአስተዋዮች ተግሳጽ (እና ትምህርት ሰጭ) ነው፡፡…” (ዩሱፍ÷ 111)


ታሪክ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ገልፀናል፡፡ ነገር ግን ታሪክን አለማወቅ አልያም እያወቁ ከርሱ አለመማር በተቃራኒው ለውድቀት ይዳርጋል፡፡ እያወቁም ይሁን ሳያውቁ የትናንት ባለጊዜዎችና የዛሬ ባለታሪኮች ከወደቁበት መውደቅን ያስከትላል፡፡ ለምሳሌ ፊርዐውንና አጋሮቹ በሕይወት ዘመናቸው እብሪታቸው ጥግ የደረሰ ነበር፡፡ “ያለኛ ማን አለ?” በማለት ድንበርን ያለፉ ነበሩ፡፡ በዚሁ ፍኖታቸው አማኞችን አውከዋል፡፡ ዘርፈ ብዙ በደሎችን ፈጽመዋል፡፡ ራሳቸውን ኃያልና የማይሸነፉ አድርገው በመቁጠር ወሰንን ሁሉ አልፈዋል፡፡ በዘመናቸው አይነኬና ፈጽሞ የማይሸነፉ ይመስሉም ነበር፡፡ ግና በበደላቸው ምክንያት አላህ አጠፋቸው፡፡ “ያለኛ ማን አለ?” እንዳላሉ ሁሉ “ነበሩ” በሚል ታሪክ ሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ስለ አማጽያን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ 


         “…(አመፀኞች) ‘ታሪክ ሆነው እንዲቀሩም አደረግናቸው፡፡…’” (አል-ሙእሚኑን÷ 44) 

በሕይወት ዘመናቸው የሕዝቡ ሁሉ የትኩረት ማዕከል ነበሩ፡፡ ስለነርሱ ጀሌዎቻቸው በቅጥፈትና ማታለያ የተሞሉ ኘሮፖጋንዳዎችን በየመንደሩ እየተዘዋወሩ ይነዙ ነበር፡፡ ለውድቀት ከተዳረጉ በኋላ ግን ያ ሁሉ እብሪታቸው ከንቱ ሆኖ ቀረ፡፡ ከውድቀታቸው በኋላ እንደከዚህ ቀደሙ ሊወደሱ ይቅርና የሚያስታውሳቸው ጠፋ፡፡ ስለነርሱ በሹክሹክታ እንኳ የሚያወሳ አልተገኘም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፦ 

    “ከነርሱ በፊት በርካታ ትውልዶችን አጥፍተናል፡፡ ከነርሱ ውስጥ አንዳቸውንም ታገኛለህን? ወይስ (ስለነርሱ) ሹክሹክታን (እንኳ) ትሰማለህን?” (መርየም÷ 98)


ታሪክን የሚያውቁ የስኬት ባለቤቶችን ጐዳና ይከተላሉ፡፡ ሙሴና በቅን የተከተሉት አማኞች በተጓዙበት ፍኖት ተጉዘው ለስኬት ይበቃሉ፡፡ እነርሱን አርኣያ አድርገው ይይዙዋቸዋል፡፡ እነ ሙሴ መልካም ጐዳናን ተከትለው የአምላክን ውዴታ እንደተጐናጸፉት እነርሱም መልካም በመሥራት የአላህን ውዴታ ይጐናፀፋሉ፡፡ የሙሳና የወንድሙ የሃሩን ታሪክ በቀጣዮቹ ትውልዶች ሁሉ እንዲዘከር መደረጉም አርኣያ እንዲሆኑን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እነርሱን እንዲህ ሲል አወድሷቸዋል፦ 


   “ለሙሳና ለሃሩንም ችሮታችንን ለገስን፡፡ እነርሱንም ሕዝባቸውንም ከከባድ ጭንቅ ነጻ አደረግን፡፡ ረዳናቸውም፡፡ በመሆኑም አሸናፊዎች ሆኑ፡፡ ግልጽ የተደረገን መጽሐፍም (ኦሪትን) ሰጠናቸው፡፡ ቀጥተኛውን ጐዳናም መራናቸው፡፡ (መልካም ሥራቸው) በቀጣዮቹ ትውልዶች ውስጥ ሲዘከር የሚኖር ይሆን ዘንድም ፈቀድን፡፡ በሙሳና በሃሩን ላይ የአላህ ሰላም ይስፈን፡፡ እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡ እነርሱ ከአማኝ አገልጋዮቻችን ናቸው፡፡” (አስ-ሷፍፋት÷ 114-122)


ከዚህ የቁርኣን አንቀጽ እንደምንረዳው የነሙሳን ፈለግ መከተል እነርሱ እንደተመነዱት በአላህ ያስመነዳል፡፡ ቀጥተኛውንም ጐዳና ያስመራል፡፡ የአላህንም እርዳታ ያስገኛል፡፡ የመልካም ታሪክ ባለቤትም ያደርጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) “እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን” በማለት ይህንኑ ገልጿል፡፡


ታሪክን የማያውቁ አልያም ሊማሩበት ያልፈቀዱት ግን የስኬት ባለቤት የሆኑትን የነሙሳንና መሰሎቹን መንገድ ሳይሆን የእኩያንን ፈለግ ይከተላሉ፡፡ ይህን በማድረጋቸውም ራሳቸውን ለውድቀት ይዳርጋሉ፡፡ ባለማወቃቸው አልያም ከታሪክ ባለመማራቸው ከአላህ ተአምራት ይዘናጋሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በአምባገነኑ ፊርዐውን ላይ ያሳረፈውን ጥቃት ቸል ይላሉ፡፡ የብዙ አምባገነኖች ችግር ይህ ነው፡፡ ከፊርዐውን ውድቀት አለመማርና በርሱ የጥፋት ጐዳና ማቅናት እጣ ፈንታቸው ሆነ፡፡ 


አላህ (ሱ.ወ) አምባገነኑን ፊርዐውንን በገደለበት ጊዜ ለራሱ ለፊርዐውን ፍጻሜውን ነግሮት ነበር፡፡ ሰዎች ከርሱ ውድቀት እንዲማሩም አስክሬኑ (አካሉ) ሳይበላሽ ለቀጣዮቹ ትውልዶች እንዲቆይም አደረገ፡፡ በመሆኑም ፊርዐውን ከሞተ ሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ቢሆነውም÷ ዛሬም ድረስ ከርሱ ታሪክ እንድንማር አካሉ ሳይፈርስ እንዲቆይ አላህ አድርጐታል፡፡ “አምላክ ነኝ” ያለው አምባገነኑ ፊርዐውን ዛሬም ድረስ በግብጽ ሙዚየም አስክሬኑ ሳይፈርስ ለታሪክ ተቀምጦ ይጐበኛል፡፡ ግና ብዙዎቹ ሰዎች ከዚህ የአላህ ተአምር ተዘናግተዋል፡፡ ሁሉን አዋቂ የሆነው አላህ (ሱ.ወ) ይህንኑ እንዲህ በማለት ቀደም ብሎ ገልጾት ነበር፦ 


     “ዛሬ÷ ከአንተ በኋላ ለሚመጡ (ትውልዶች) ተአምር ትሆን ዘንድ÷ አካልህን እናድናለን፡፡ ግና ብዙዎቹ ሰዎች ተአምራቶቻችንን ይዘነጋሉ፡፡” (ዩኑስ÷ 92) 


ዛሬም ድረስ በርካቶች የፊርዐውንን ፈለግ እየተከተሉ ነው፡፡ እርሱ ለውድቀት እንደተዳረገውም እነርሱም ለውድቀት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ በተመሳሳይ ፈለግ እያቀኑ የተለየ ውጤት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ፊርዐውንም ለውድቀት የተዳረገው “ፊርዐውን” ስለሆነ ሳይሆን በእኩይ ተግባሩና ማንነቱ ምክንያት ነበር፡፡ የርሱን ፈለግ በመከተል አምባገነን የሆኑትም እንደርሱ የውድቀትና የጥፋት ፍፃሜ ይኖራቸዋል፡፡ ይህ አንዱን አምባገነን ከሌላው የሚለይ አይደለም፡፡ ሁሉንም አፈንጋጮችና አምባገነኖችን የሚጠብቃቸው እውነት ነው፡፡ ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ሲል ግልጽ ያደረገው፦ 


   “አምባገነንና አፈንጋጭ የሆነ ሁሉም ፍጻሜው ውድቀት ሆነ፡፡”(ኢብራሂም÷15)


  ፊርዐውንና አጋሮቹን ቁርኣን የአምባገነኖች ምሳሌ አድርጐ ያቀረበው ከነርሱ ትምህርት እንዲወሰድ ነበር፡፡ ግና ይህንኑ ምሳሌ በመዘናጋት÷ ቸል በማለትና ባለመቀበል የጥፋትንና የአምባገነንነትን ጐዳና ብዙዎች እየተከተሉ ነው፡፡ ቅኑን ጐዳና መከተልንም አሻፈረን አሉ፡፡ የአመጽንና የክህደትን ፍኖት የሙጥኝ አሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦ 


    “ለሰው ልጆች በዚህ ቁርኣን ውስጥ ምሳሌዎችን ሁሉ አብራራን፡፡ ግና ብዙዎቹ ሰዎች ክህደትን እንጂ አሻፈረን አሉ፡፡” (አል-ኢስራእ÷ 89) 


    አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ በማለት አማኞች ሙሳን እንዳወኩት ወገኖቹ እንዳይሆኑ መክሯል፦ 


    “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እንደነዚያ ሙሳን እንዳወኩት አትሁኑ፡፡ ግና አላህ ካሉት ነገር አጠራው፡፡ከአላህ ዘንድ ክብር የተቸረው ሰው ነበርና፡፡” (አል-አሕዛብ÷69) 


በተጨማሪም ቁርኣን የአምባገነኖችንና የወሰን አላፊዎችን ትዕዛዝ መከተልን ከልክሏል፡፡ እንዲህም ብሏል፦ 


   “‘የወሰን አላፊዎችንም ትዕዛዝ አትከተሉ፡፡ የነዚያን ምድር ላይ ብክለትን የሚያስፋፉትንና የሚበጅ ነገር የማይፈጽሙትን’ (አላቸውም)፡፡” (አሽ-ሹዐራእ÷151-152)


       እስካሁን በስፋትና በጥልቀት የፊርዐውን ተከታዮችን የጥፋት ጐዳና ዳስሰናል፡፡ እኩዩን ፍኖታቸውን ግልጽ ለማድረግም ተሞክሯል፡፡ የዚህ ሁሉ ሀተታ ማጠንጠኛ የአፈንጋጮችን የጥፋት ፍኖት ግልጽ በማድረግ ትምህርት እንዲቀሰምበት ማስቻል ነው፡፡ ቁርኣንም ታሪኩን የተረከልን ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ እንዲህም ይላል፦ 


   “የአፈንጋጮች ፍኖት ግልጽ ይሆን ዘንድ አንቀጾችን በዚህ መልኩ እናብራራለን፡፡” (አል-አንዓም÷ 55)


    መጽሐፉንም በቀጣዩ የአላህ ቃል እናሳርጋለን፦ 

    ‹‹ከነርሱ በፊት÷ በኃይል ከነርሱ ይበልጥ ብርቱ የነበሩ ትውልዶችን አጥፍተናል፡፡ (ከጥፋት ለማምለጥ) በየሀገሩ ተንከራተቱ፡፡ ግና ማምለጫ ነበራቸውን? (አስተዋይ) ልቦና ላለው÷ (ተግሳጽንም ለማድመጥ) ጆሮውን ለከፈተ÷(እውነትን) ለመሰከረም በዚህ ውስጥ ተግሳጽ አለበት፡፡››(ቃፍ÷ 36-37) 


     ‹‹ምድር ላይ ለተጨቆኑ ሕዝቦች (ፀጋዎችን) ልንለግሳቸው፤ መሪዎችም ልናደርጋቸው፤ ወራሾችም ልናደርጋቸው ከጀልን፡፡ ምድር ላይም ምቾትን ልንለግሳቸው ለፊርዐውን፣ ለሃማንና ሠራዊቶቻቸው ይፈሩት የነበረውን ልናሳያቸው (ፈቀድን)፡፡›› (አል-ቀሰስ÷ 5-6) ››


(አህመዲን ጀበል፣ፈርዖን የአምባገነኖች ተምሳሌት፣ 2007፣ቃሊቲ ማረሚያ ቤት፣ገጽ 364-369)

★★★★★★★★★★★★★

ከታሪክ ማህደር


Comments

Popular posts from this blog

Seenaa Motummaa Jimmaa (kutaa 1ffaa)

The Untold Story of the Battle of Maqdala and the Struggle Between Emperor Tewodros and the Oromos