ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው» ክፍል 2
«ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው»
ክፍል 2: በኡስታዝ አሕመዲን ጀበል
❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄
የሀገራችንን የአማርኛ ሚዲያዎች ተቆጣጥረው እንዳሻቸው የሚዘውሩት የሰጠመችው ደሴት ናፋቂዎች «ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው» የሚል ሰነድ በማጋራትና ይህንኑ መነሻ በማድረግ በእኔ ላይ ከጀመሩት የስም ማጥፋት ዘመቻ ጋር ተያይዞ ንጹሃንና የዋሆችን ለመታደግ ስል ብቻ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሀሳቤን እያጋሯኋችሁ እገኛለሁ።
በክፍል አንድ በርካታ ነጥቦችን ዳሰናል። በዚህ ክፍል ደግሞ «ሚዲያን ስለመቆጣጠር» ጉዳይና ስለስልጠናው አብረን እንመለከታለን። ሀሳቡ ለሌሎች እንዲደርስ በማንኛውም መንገድ ሼር በማድረግ የበኩልዎን ሚና እንዲወጡ እየጋበዝኩ ሀሳቤን እቀጥላለሁ።
✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺✺
«ጠንቃቃ ካልሆንክ ጋዜጦች የተበደሉትን እንድትጠላና በዳዮችን እንድትወድ ሊያደርጉህ ይችላሉ።» (ማልኮም ኤክስ)
✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸✸
«ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው» የሚለውን ቁንጽል ሀሳብ ይዘው እንደነውር ለማሳየት የሚጥሩት አካላት ሆን ብለው የዘነጉት ነገር እንዳለ እናስተውል። የሰውን ሐሳብ ለመቆጣጠር (ማኑፑሌት ለማድረግ) በሚጥሩ ሚዲያዎች መካከል ማህበረሰቦች ራሳቸውን ሊከላከሉና የሚዲያ ጥምዘዛን ሊቋቋሙ የሚችሉት ጠንካራ ሚዲያ ሲኖራቸው ነው። ከዚህ አንጻር «ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው» የሚለው ንግግር የሚዲያን ኃይል ማስጠንቀቂያ እንጂ የግድ ሰዎችን የመቆጣጠር ሙከራ ነው ማለት አይደለም።
ሚዲያዎችን በመቆጣጠር የህዝብን አመለካከት የመቆጣጠሩ ፋሽን ምን ያክል ተጨባጭ እውነታ እንደሆነ ለማየት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የአሜሪካ ሚዲያዎችን በባለቤትነት የተቆጣጠሩት አካላት ማንነት ነው። በአሜሪካ ከዲጂታል እስከ ህትመት፣ ከራዲዮ እስከ ቲቪ፣ ከጋዜጣ እስከ መጽሄት፣ ከሲኒማ እስከ ካርቱን፣ ከቶክሾው እስከ ዶኩመንተሪ፣ ከሆሊዉድ እስከ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከምግብ ዝግጅት እስከ ፖለቲካ፣ ከዜና እስከ ስፖርት ያሉ እጅግ የተራራቁ የሚመስሉ ዘርፎች በመሰማራት የአሜሪካውያን ቤቶች መቶ በመቶ የሚሸፍኑ ሚዲያዎች በጥቂ አካላት ባለቤትነት የተያዙ ናቸው።
በ1980 የአሜሪካ ሚዲያዎችን በባለቤትነት ተቆጣጥረው የነበሩት 50 ድርጅቶች ነበሩ። በ1990 ደግሞ ድርጅቶቹ ከ50 ወደ አምስት ዝቅ አሉ። በ1990ዎቹ መጀመሪያ የአሜሪካን ዘጠና በመቶ ሚዲያዎች በባለቤትን የተቆጣጠሩት አምስት ግዙፍ ድርጅቶች ናቸው። (Comcast, The Walt Disney Company, Warner Bros. Discovery, and Paramount Global) የተቀረውን 10 በመቶ የያዙት ሌሎች ትናንሽ ድርጅቶች ናቸው።
ድርጅቶቹ የተሰማሩት በተለያዩ ስሞችና ዘርፎች፣ በተለያዩ አቀራረቦች፣ በተለያዩ ትኩረቶችና ውግንናዎች ቢመስልም ብዙ ሰው በማይጠረጥርበት ሁኔታ 90 በመቶው ከአምስቱ ግዙፍ ድርጅቶች በአንዱ ባለቤትነት የሚያዙበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። ይህ አቀራረባቸው ሕዝቡ የትኛውንም ሚዲያ ቢከታተል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከነርሱ ተጽዕኖ ነጻ መሆን እንዳይችል አድርጎታል።
ለኮንግረንስ፣ ለሴኔት፣ ለአስተዳዳሪነት ወይም ፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚፈልግ አካል የሕዝቡን ድምጽ ለማግኘት ሳይወድ በግዱ የግዙፎቹ የሚዲያ ባለቤቶች ደጅ ለመጥናት ይገደዳል። ወደ ስልጣን ሲመጣ በምን መልኩና ምን ያክል የነሱን ፍላጎትን ለማስጸም እንደሚችል ገልጾ ይደራደራል።
እነሱ እንዲወጣ ወይም እንዲሰረዝ የሚፈልጉትን ሕግ፣ መመሪያና አሰራር በጥቅሉ ከእነሱ ጥቅምና ፍላጎት አንጻር የሚሆናቸውን አካል በሚዲያ ሽፋንና ድጋፍ በመስጠት፣ ጎላ ብሎ እንዲታይና መልካም ስምና ገጽታ እንዲኖረው ይሰራሉ። ተቀናቃኞቹን ደግሞ ስምና ዝናቸውን በማጉደፍ፣ አሳንሶ በማሳየትና ተቀባይነት እንዳያገኙ በማድረግ ከምርጫው በሽንፈት እንዲወጡ ያደርጋሉ። ንጹሃንን እንደ ወንጀለኛ፣ ወንጀለኛውን እንደ ንጹህና መልካም ሰው አድርገው ያቀርባሉ። በተለያዩ መንገዶች የእነሱን ሀሳብ በህዝቡ ውስጥ በማስረጽ ፍላጎቶቻቸውን በሕዝቡ ላይ ይጭናሉ። ከፍላጎቶቻቸው በተቃራኒ ሲቆም ሕዝብን በመንግስት ላይ በማስነሳትና ጫና በመፍጠር የመንግስትን እጅ ይጠመዝዛሉ።
የእኛም አገር የአማርኛ ሚዲያ ከቀደሙ ስርዓቶች ያገኙትን በሚዲያው ውስጥ ቀድሞ ቦታ የመያዝ ዕድል ተጠቅመው አጀንዳቸውን ማስፈጸም፣ የህዝቡን ስሜት ተቆጣጥሮ መያዝና ማጠልሸት የፈለጉትን የማጠልሸቱ ተጨባጭ በስፋት የሚታይ ነው። የበለጠ የሚገርመው ደግሞ እዚሁ ውስጥ ዋና ሚና የሚወጡት እኔኑ ለማጠልሸት እየጣሩ ያሉት አካላት ራሳቸው መሆናቸው ነው የሚገርመው።
ከዚህ እውነታ አንጻር የሚዲያን ዓለምአቀፋዊ ኃይል እና የህዝብን አዕምሮ ተቆጣጥሮ የፈለጉትን የማስፈጸም ኃይል መጎናጸፋቸውን በማሳየት ማህበረሰቦች እና ቡድኖች እውነታውን ተረድተው ለሚዲያ ማኑፑሌሽን በማይመች መልኩ ራሳቸውን እንዲያጠነክሩ፣ የቆሙለትን ዓላማ በህዝቡ ዘንድ ለማስረጽ በዚህ ችሎታ እንዲያዳብሩ ማነሳሳት ተጨባጭን መረዳት እንጂ መጥፎ ተግባር አይደለም።
ያስበረገጋቸው የሚዲያ ስልጠና ጉዳይ
❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄❄
ባለፉት14 ዓመታት ከተለያዩ ሀገራት በሚሰጡ የፕሮፌሽናል ክህሎት ስልጠናዎች የመሳተፍ እድል አግኝቻለሁ። ከኢትዮጵያ እስከ እንግሊዝ፣ ከኤዥያ እስከ አፍሪካ፣ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ወዘተ የሚዲያና የሌሎች ክህሎቶች ስልጠና በአካልም ሆነ በኢንተርኔት ወስጃለሁ። ምስጋና ለአላህ ይገባውና እድሉን ካገኘሁ ወደፊትም ገና እወስዳለሁ።
ከእነዚህ ስልጠናዎች ያገኘኋቸውን ክህሎቶችና ተሞክሮዎች በማከል ለሙስሊም ወገኖቼ በኢንተርኔትም በአካልም ሰጥቻለሁ። የሚዲያ ስልጠና መሰጠቱ የገረማቸው የሰጠመችው ደሴት ናፋቂዎች እርማቸውን ቢያወጡ ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም አላህ ከፈቀደ ወደፊትም ብዙ ስልጠና መስጠቴ አይቀርም።
«ሚስጥራዊ የሽብር ስልጠና» ወዘተ የሚሉ አጠልሺ ታፔላዎች ተለጥፎባቸው በከባድ ሚስጢር የወጡ ተመስለው የተለቀቁትን ሰነዶችን በማየት ጥቂትም ቢሆን ጥርጣሬ የገባቸው ካሉ ስለሰነዶቹ ጥቂት ማለቴ አይከፋም። ለአውቆ አጥፊዎቹ የሚዲያ ቆማሪዎች ቦታም ሰጥቶ ምላሽ መስጠት እንደማይገባ ባምንም «ሰነዶቹ የማን ናቸው? በማንና እንዴት ተዘጋጁ?» የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሯቸው ለሚመላለስባቸው እውነት ፈላጊዎች ስል ነው እንደሚከተለው የማብራራው።
ለሙከራ ከሰጠሁት የሚዲያ ስልጠና ላይ ሰልጣኞች የሚዲያን ኃይልና ተጽዕኖ እንዲረዱ በተሰጣቸው ስልጠና ፍጸሜ ላይ ከተማሩት በመነሳት የቡድን ሥራ ተሰጣቸው። ለቡድን ስራ ከተሰጡት ርዕሶች አንዱ ደግሞ «ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው» የሚለውን የተግባበቦት ሊቃውንት ጥቅስ ማብራራት ነበር። ለሰልጣኞች በቡድን የሚሰሩትን የቤት ስራ እንዲሰሩ መግለጫ ጽሑፍ ተለጠፈላቸው። የቡድን ስራዉን ሲሰሩ የአሜሪካ ሚዲያዎች እንዴት በ5 ደርጅቶች ቁጥጥር ስር እንደሆኑ የሚያሳየውን «Capitalism And Monopolies፡ How Five Companies Control All US Media» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የዩቲዩብ ቪዲዮ በመነሻነት እንዲመለከቱ ተያያዘላቸው። ለቡድን ስራቸውም ቀጥሎ ያለው መመሪያ ተሰጣቸው... (የመመሪያው ስክሪንሾት ከነርዕሱና ከነቀኑ ከስር ተያይዟል) እንዲህ ይላል...
«አሰላሙ ዓለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱሁ! ሚዲያን መቆጣጠር ምን ያክል ሀገርን መቆጣጠር መሆኑን «Capitalism And Monopolies፡ How Five Companies Control All US Media» የሚለውን ይህን አጭር ቪዲዮ በመመልከት የሀገራችን የሚዲያ ሁኔታ ላይ ውይይት በማድረግ የሀገራችን ሙስሊም ያልሆኑ አካላት ተጽዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊና የመደበኛ ሚዲያዎችን ከቆሙለት አካልና ከሚያቀነቅኑት አጀንዳዎች በመነሳት የአሰላለፍ ሁኔታቸውን፥ መረዳት እስከ ተቻለ ድረስ የእነማን እንደሆኑ የመለየት የቡድን ስራ ትሰራላችሁ። ለቡድን ስራው የአክቲቪዝም የቤት ስራዎችን የሰራችሁበትን ቡድን ትጠቀማላችሁ። የቡድናችሁንም ሪፖርት የፊታችን ጁሙዓ ድረስ ማስረከብ ይገባችኋል።»
ቀጥሎም ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር መሆኑን እንዲረዱ ለግንዛቤ ያክል ቀጥሎ የሚገኘው ጽሑፍ ተለጠፈላቸው...
“(ለግንዛቤ ያክል)...
የሚዲያ የበላይነትን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር ነው (ሲባል)
1/ የሚዲያ የበላይነትን መቆጣጠር ማለት ወደ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚደርሱትን መረጃዎችን መቆጣጠር ማለት ነው
2/ ወደ ዓይንና ጆሮ የሚደርሱትን መረጃዎችን መቆጣጠር ደግሞ ወደ ስው አዕምሮ ዉስጥ የሚከማቹትን መረጃዎች መቆጣጠር ማለት ነው፤
3/ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የሚከማቹትን መረጃዎች መቆጣጠር ማለት ደግሞ አዕምሮ ለማሰብ ሂደት በግብዓት የሚጠቀማቸውን መረጃዎች መቆጣጠር ማለት ነው፤
4/ አዕምሮ በግብዓትነት ተጠቅሞ የሚያስባቸውን መረጃዎች መቆጣጠር ማለት አዕምሮ ስለምን ጉዳይ እንደሚያስብ መቆጣጠር ማለት ነው፤
5/ በሚዲያ አማካኝነት የዘገባዎችን ቅኝት (frame) የበላይነት መቆጣጠር ማለት ደግሞ እንዴት እንደሚያስቡ አስተሳሰባቸውን መቆጣጠር ማለት ነው፤
6/ ሰዎች ስለምንና እንዴት እንደሚያስቡ መቆጣጠርና መወሰን መቻል ማለት ደግሞ የሰዎችን አስተሳሰብና ሀሳብ መቆጣጠር መቻል ማለት ነው፤
7/ አስተሳሰብን (እንዴት እንደሚያስብ) እና ሀሳብን መቆጣጠር ማለት ደግሞ የሕዝቡን አመለካከትና እምነትን መቆጣጠር ማለት ነው፤
8/ አመለካከትና እምነትን መቆጣጣር ማለት ደግሞ የሰዎችን ውሳኔ መቆጣጠር ማለት ነው፤
9/ የሰዎችን ውሳኔ መቆጣጠር ማለት የሰዎችን ድርጊት መቆጣጠር ማለት ነው፤
10/ የሰዎችን ድርጊት መቆጣ ጠር ማለት ደግሞ ሰዎችን መቆጣጠር መቻል ማለት ነው፤
11/ ሰዎችን መቆጣጠር ማለት በሰዎች ላይ ኃይልን መጎናጸፍ መቻል ማለት ነው፤
12/ የሚዲያን የበላይነትን የተቆጣጠረ አካል ሕዝብን ተቆጣጠረ ማለት ነው፤
13/ ሕዝብን የተቆጣጠረ አካል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሀገርን ተቆጣጠረ ማለት ነው፤
14/ ለዚህም ነው ሚዲያ ወሳኝ ከሚባሉ የኃይል መሠረቶች መካከል አንዱ የሆነው፤
በዚህ መነሻነት ሰልጣኞች በተሰጣቸው የቡድን ስራ ላይ የሚሰማቸውን ምላሽ ከራሳቸው አስተሳሰብ እና መረጃ ተነስተው አመለካከታቸውን «ለሕመዲን ጀበል» ብለው ጻፉ። የሰነዶቹ አመጣጥ ይህን ይመስል ነበር።
በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ተከታዮቼ ልክ ሰልጣኞቹ እንዳደረጉት ከዚህ ጽሑፍና ሰልጣኞች እንዲመለከቱ ተያያዞላቸው ከነበረው የእንግሊዝኛ ቪዲዮ አንጻር (ቪዲዮው ከታች ተያይዟል) በሀገራችን የሚዲያ ሁኔታ ላይ ውይይት እንድታደርጉ እጋብዛለሁ። የሀገራችን ሙስሊም ያልሆኑ አካላት ተጽዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊና የመደበኛ ሚዲያዎችን ከቆሙለት አካልና ከሚያቀነቅኑት አጀንዳ በመነሳት የአሰላለፍ ሁኔታቸውን፣ መረዳት እስከ ተቻለ ድረስ የእነማን እንደሆኑ ጭምር በመለየት ተሳተፉ። ሚዲያን መቆጣጠር ሀገርን መቆጣጠር» በሚል በተነሳው ባለ 14 ነጥብ ሀሳብ ላይም የሚሰማችሁን ሀሳቦቻችሁን በነጻነት አጋሩን። በያላችሁበትም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ተወያዩ። በውጭ አገራት ሚዲያዎችን በተለያዩ መስመሮች አይደንቲፋይ አድርጎ አሰላለፋቸውን የመረዳት ጉዳይ የተለመደና በየጊዜው የሚሰራ ነው። እኛም ብናደርገው አረዳዳችን የበለጠ ያዳብርልናል። ጠንካራ እና አጀንዳ ቀራጭ ሚዲያ እንድናቋቁም ማበረታቻ ይሆነናል።
ይቀጥላል…
Ahmedin jabal
ReplyDelete